በፈረሰኞቹ በኩል በላፈዉ ሳምንት ጨዋታ ከተጠቀሟቸዉ ቋሚ አስራአንድ ተገኑ ተሾመን በቡልቻ ሹራ ብቻ ቀይረዉ ለዛሬዉ ጨዋታ ሲቀርቡ በአንፃሩ በአፄዎቹ በኩል ደግሞ ተከላካዩን ከድር ኩልባሊ በያሬድ ባየ እንዲሁም ሀብታሙ ተከስተን በይሁን እንዳሻዉ ቀይረዉ ወደ ሜዳ ገብተዋል።
በማረ የደጋፊዎች ድባብ የጀመረው የሁለቱ ክለቦች ጨዋታም ገና በጊዜ ነበር ግብ የተስተናገደበት ፤ በ5ኛዉ ደቂቃ ለይ በግራ መስመር በኩል ከአምሳሉ ጥላሁን የተቀበለውን ኳስ በግሩም ዕይታ እና በድንቅ ብቃት በዛብህ መለዮ ለአጥቂዉ ኦኪኪ አፎላቢ አቀብሎት አጥቂዉ ኳሷን ከተቆጣጠረ በኋላ ወደ ግብነት በመቀየር ገና በጊዜ ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል።
ከግቧ መቆጠር በኋላ በሁለቱ ክለቦች በኩል በተደጋጋሚ ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል ለመድረስ ከሚደረጉ ጥረቶች ዉጭ ሌላ አደገኛ ሙከራን የተመለከትነዉ በ29ኛዉ ደቂቃ ላይ ነበር የመስመር ተከላካዩ ሱለይማን ሀሚድን ለማሻማት ብሎ ወደ ግብ የላካት ኳስ ጥሩ አቋቋም ላይ ያልነበረዉን ሚኬል ሳማኪ አልፋ ለጥቂት በግቡ አናት ላይ የወጣችዉ ኳስ በፈረሰኞቹ በኩል ሌላ አስቆጭ አጋጣሚ ነበረች።
በተደጋጋሚ ጥፋቶች ይሰሩበት በነበረዉ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በጥሩ የአጨዋወት መንገድ ወደ አፄዎቹ የግብ ክልል ለመድረስ ሲሞክሩ ፤ በተቃራኒው አፄዎቹ መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ ካስቆጠሩ በኋላ በይበልጥ ወደ ራሳቸዉ የግብ ክልል ተደራጅተው በመከላከል እና አልፎ አልፎ በሚገኙ ኳሶች በመልሶ ማጥቃት አስደንጋጭ ሙከራዎች ለማድረግ ሲታትሩ ተመልክተናል።
በተለይ በ41ኛዉ ደቂቃ ላይ ከመሐል ሜዳ በረጅሙ የተሻገረለትን ኳስ ኦኪኪ አፎላቢ ከፈረሰኞቹ ተከላካይ ፍሪምፖንግ ሜንሱ ጋር እየታገለ ሳጥን ዉስጥ ከደረሰ በኋላ ወደ ግብ ሲሞክር ሌላኛው ተከላካይ ምኞት ደበበ ደርሶበት ተደርቦ ሲያወጣበት በድጋሚ ያገኘዉ ኦኪኪ አሁንም ሲሞክር ተደርበዉ አዉጥተዉበታል በዚህ ሁነት ላይም ኦኪኪ ጥፉት ተሰርቶብኛል ብሎ ቢወድቅም የዕለቱ ዳኛ በዝምታ ያለፉት ክስተት ተመልካቹን ቁጭ ብድግ ያስባለ ነበር።
በአንፃሩ ፈረሰኞቹ በተደጋጋሚ በግራ መስመር በኩል በቸርነት ጉግሳ ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴን ቢያደርጉም ግብ ማግኘት ሳይችሉ የመጀመሪያው አጋማሽ በአፄዎቹ መሪነት ተጠናቋል።
ከዕረፍት መልስ ከንዓን ማርክነህን እና አቤል ያለዉን በያብስራ ተስፋየ እና ተገኑ ተሾመ ቀይረዉ ወደ ሜዳ ያስገቡት ፈረሸኞቹ ተደጋጋሚ የግብ ዕድሎችን አግኝተዉ የነበረ ቢሆንም ግን ሳይጠቀሙባቸዉ ቀርተዋል።
በዚህ ሂደት በቀጠለዉ ጨዋታም በአፄዎቹ በኩል ሌላ ለግብ የቀረበ ሙከራን ተመልክተናል። በ50ኛዉ ደቂቃ ላይ ሱራፌል ዳኛቸዉ ከመዓዘን ያሻገራት ኳስ ተጨራርፋ ስትመጣ በዛብህ መለዮ አግኝቷት አስቆጭ ሙከራ ማድረግ ችሎ ነበር።
በ58ኛዉ ደቂቃ ላይ የፈረሰኞቹ አምበል ሀይደር ሸረፋ የቀኝ ጎኑ አካባቢ ጉዳት በማስተናገዱ ምክንያት እሱን ተክቶ ናትናኤል ዘለቀ ወደ ሜዳ ሲገባ በአንፃሩ በአፄዎቹ በኩል እየተቀየረ በመግባት ክለቡን የሚታደገዉ ፍቃዱ አለሙ ኦኪኪ አፎላቢን ተክቶ ገብቷል።
የጨዋታዉ ሰዓት እየገፋ በመጣ ቁጥር የማጥቃት ፍላጎታቸዉ እየጨመረ የመጡት ፈረሰኞቹ በ66ኛዉ ደቂቃ ላይ ያገኙትን የቅጣት ምት ሄኖክ አዱኛ ቀጥታ ወደ ግብ ሞክሯት የነበረ ቢሆንም የገብ ዘቡ ሳማኪ እንደምንም አዉጥቷታል። ፈረሰኞቹ በተደጋጋሚ በአማካዩ ጋቶች ፓኖም በመስመር አጥቂዎቹ ቸርነት ጉግሳ እና አቤል ያለዉ ሙከራዎችን ማድረግ ቢችሉም በዕለቱ ድንቅ በነበረዉ የግብ ዘቡ ሚኬል ሳማኪ ምክንያቶ ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተዉ ከ24 ጨዋታዎች በኋላ በዉድድር አመቱ የመጀመሪያውን ሽንፈት አስተናግደዋል።
አሁንም ቅዱስ ጊዮርጊስ በ54 ነጥብ የሊጉ መሪ ሲሆን አፄዎቹ በ49 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ በቀጣይም ፋሲል ከነማ ከሰበታ ከተማ እንዲሁም ቅዱስ ጊዮርጊስ ከባህርዳር ከተማ የሚገናኙ ይሆናል።
0 Comments
HABESHAWI SPORT