የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር አመራርና ስነ-ስርዓት ኮሚቴ ማክሰኞ ግንቦት 16 2014 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ በተደረጉ የፕሪሚየር ሊግ ግጥሚያ(ዎች) ከዳኞች እና ከታዛቢዎች የቀረቡለትን የዲሲፕሊን ሪፖርት ከመረመረ በኋላ የተለያዩ የዲሲፕሊን ውሳኔዎችን አስተላልፏል።
በተጫዋቾች ወንድማገኝ ማርቆስ(ጅማ አባ ጅፋር)፣ አንተነህ ጉግሳ(ወላይታ ድቻ)፣ በኃይሉ ግርማ(ሰበታ ከተማ) እና አዲስዓለም ተስፋዬ(ሃዋሳ ከተማ) በተለያዩ የክለባቸው ጨዋታዎች አምስተኛ ቢጫ ካርድ በማየታቸው ለፈፀሙት ጥፋት በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት 1 ጨዋታ እንዲታገዱና በተጨማሪ የገንዘብ ቅጣት ብር 1,500 /አንድ ሺ አምስት መቶ/ እንዲከፍሉ እንዲሁም ፍሬዘር ካሳ(ሀዲያ ሆሳዕና)፣ ጊት ጋትኩት(ሲዳማ ቡና)፣ በረከት ሳሙኤል (ሰበታ ከተማ) እና ሚሊዮን ሰለሞን(አዳማ ከተማ) አስረኛ ቢጫ ካርድ በመመልከታቸው ሁለት ጨዋታ እንዲታገዱና የገንዘብ ቅጣት ብር 2,000 /ሁለት ሺህ/ እንዲከፍሉ ውሳኔ ተላልፏል። በተጨማሪም ዳዋ ሆጤሳ (አዳማ ከተማ) የተጋጣሚን ቡድን አፀያፊ ስድብ በመሳድብ ከጨዋታ ሜዳ የተወገደ ስለመሆኑ ሪፖርት የቀረበበት 3 ጨዋታ እንዲታገድና የገንዘብ ቅጣት ብር 3,000 /ሶስት ሺ/ እንዲከፍል ፥ ጌታነህ ከበደ(ወልቂጤ ከተማ) የዕለቱ ጨዋታ ካለቀ በኋላ የውድድር አመራሮችን አፀያፊ ስድብ ስለመሳደቡና ስለመዝለፉ ሪፖርት የቀረበበት በፈፀመው ጥፋት በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት 3/ሶስት/ ጨዋታ እና ብር የ3,000 /ሶስት ሺህ/ እንዲቀጡ ተወስኗል።
በክለቦች ደረጃ የአዳማ ከተማ ክለብ 7 ተጫዋቾች እንዲሁም የሲዳማ ቡና ክለብ 6 ተጫዋቾች በተለያዩ ጥፋቶች ካርድ የተሰጣቸው በመሆኑ የገንዘብ ቅጣት ብር 5,000 /አምስት ሺ/ እንዲከፍሉ ፥ ባህር ዳር ከተማ በሳምንቱ ጨዋታ የክለቡ ደጋፊዎች ጨዋታው ካለቀ በኋላ የክለቡን አመራሮችና ተጫዋቾች በተደጋጋሚ አፀያፊ ስደብ ስለመሳደባቸው ሪፖርት የቀረበበትና እንዲሁም ከዚህ በፊት ተመሳሳይ ጥፋት አጥፍተው የተቀጡና በዚህም ደጋፊዎቹ ከድርጊታቸው አለመማራቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት ብር የ75,000 /ሰባ አምስት ሺህ/ እንዲቀጣ ፥ ፋሲል ከነማም የክለቡ ደጋፊዎች በሳምንቱ ጨዋታቸው የዕረፍት ሰዓት ወቅት ፖለቲካዊ ይዘት ያለው መልዕክት ስለማስተላለፋቸው እንዲሁም የዕለቱ ጨዋታ ካለቀ በኋላ ወደሜዳ ዘለው ስለመግባታቸው ሪፖርት የቀረበበት የክለቡ ደጋፊዎች በዕለቱ በፈፀሙት ጥፋት በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት ብር 50,000 /አምሳ ሺህ/ እንዲቀጣ ተወስኗል።
0 Comments
HABESHAWI SPORT