ባህርዳር ከተማ አስተዳደር የዳኞችና ታዛቢዎች ሙያ ማህበር ለ3 ዓመት የሚቆይ የብራንድ ትጥቅ አቅርቦት ስምምነት ከአገር በቀሉ ጎፈሬ የስፖርት ትጥቅ አምራች ጋር ተፈራርሟል፡

፡ የማህበሩ ም/ፕሬዚዳንት ፌዴራል ዳኛ ሰሎሞን አጥናፉ ስምምነቱ በገበያ ላይ ያለውን የዳኞች ማጫዎቻ ትጥቅ (መለያ) የዋጋ ንረትና እጥረት በእጅጉ እንደሚፈታላቸውና አዘውትሮ በየጨዋታው የሚደረገውን የማጫዎቻ ማልያ ትጥቅ አለመመሳሰልና መዋዋስ እንደሚያስቀርላቸው እና ስምምነቱ የዳኞችን አቅም ያማከለ ሀገር በቀል መሆኑ ተመራጭ እንደሚያደርገውም ተናግረዋል ፡፡ ም/ፕሬዘዳንቱ አገር በቀሉ ጎፈሬ በጣም ወሳኝ በሆነ ወቅት በጥራትና በተመጣጣኝ ዋጋ ለማህበራቸው ብራንድ አቅራቢ ለመሆን በመስማማቱ በማህበሩ ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ የጎፈሬ ብራንድ ስፖርት ትጥቅ አምራች ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሳሙኤል መኮንን በበኩላቸው በመላ አገሪቱ የዳኞች ማጫዎቻ ትጥቅ እጥረት የፈጠረውን ችግር በጥልቀት እንደሚረዱ ገልፀው ጎፈሬ ይህንን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ዳኞችና ታዛቢዎች ማህበርን አሰራርና ቅልጥፍናን በእጅጉ ያደነቁትና ያመሰገኑት ስራ አስኪያጁ በቀጣይ በሌሎች የትጥቅ አይነቶች በጥራትና በተመጣጣኝ ዋጋ ለማህበሩ እንደሚያቀርቡላቸው ገልፀዋል፡፡ በስምምነቱ ጎፈሬ 3 ዓይነት የማጫዎቻ ትጥቅ (ማልያ) እና ሌሎች ትጥቆችን የሚያቀርብ ሲሆን ከብራንድ ትጥቅ አቅርቦት በተጨማሪ ጎፈሬ የማህበሩን እንቅስቃሴ ለማጎልበትና ለማሳደግ አብሮ ለመስራት መስማማቱ ተገልፆዋል፡፡

0 Comments