ፋሲል ከነማ በ23ኛዉ ሳምንት ባህርዳር ከተማን በረታበት ጨዋታ ከተጠቀማቸዉ ቋሚ አስራአንድ የሁለት ተጫዋቾች ለዉጥ አድርጎ ወደ ሜዳ ሲገባ በአንፃሩ መከላከያ ሲዳማ ቡናን የረታበትን ሙሉ አሰላለፍ ይዞ ወደ ሜዳ ገብቷል።
በዋና ዳኛ ኤፍሬም ደበሌ ፊሽካ የጀመረው የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ከወትሮው ለየት ባለ መልኩ ድንቅ ዕንቅስቃሴን ያስመለከተን ነበር በተለይ በጨዋታው መጀመሪያ ደቂቃ ላይ የመከላከያዉ አጥቂ እስራኤል እሸቱ ከሳጥን ዉጭ አደገኛ ሙከራ ማድረግ የቻለ ቢሆንም ግብ ጠባቂዉ ሳማኪ በግሩም ብቃት አዉጥቶታል። ከዚህ ድንቅ ሙከራ በኋላ ደግሞ ከድር ኩልባሊ ቢኒያም በላይ ላይ ጥፋት በመስራቱ ምክንያት የተገኘዉን ፍፁም ቅጣት ምት አሚን ነስሩ አስቆጥሮ ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል።
በጨዋታ የመጀመሪያ ደቂቃ ላይ ግብ ያስተናገዱት አፄዎቹ በ10ኛዉ ደቂቃ ላይ ደግሞ አቻ መሆን የቻሉበትን ግብ አስቆጥረዋል። አምሳሉ ጥላሁን ከመሀል ሜዳ ከበረከት ደስታ የተሻገረለትን ኳስ በግሩም ብቃት በመቆጣጠር ለሽመክት ጉግሳ አቀብሎት ሽመክት ወደ ግብነት በመቀየር ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል። ገና ጨዋታው በተጀመረ 10 ደቂቃ ዉስጥ ሁለት ግብ ያስመለከተን የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ መጠነኛ የሚባል ፉክክርን እያስመለከተን አጋማሹ ተጠናቋል።
በተለይ በፋሲል ከነማ በኩል የመሀል ሜዳዉን የበላይነት በመዉሰድ እና በጥሩ የጨዋታ እንቅስቃሴ ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል ለመድረስ ሲሞክሩ በአንፃሩ በመከላከያ በኩል ደግሞ የአፄዎቹን አንድ ሁለት ቅብብል በማቋረጥ በመልሶ ማጥቃት ተጨማሪ ግብ ለማግኘት ሲሞክሩ ነበር በተለይ አማካዩ ቢኒያም በላይ እና አጥቂዉ እስራእል እሸቱ ተደጋጋሚ የግብ ሙከራዎች ማድረግ የቻሉ ቢሆንም ድንቅ በነበረው የግብ ዘብ ሳማኪ ሲመክኑ ተስተውሏል።
ከአጋማሹ መልሱ በተመሳሳይ የጨዋታ መንገድ ለተመለሱት ለሁለቱ ክለቦች ጨዋታ በ74ኛዉ ደቂቃ ላይ ግብ ተስተናግዶበታል። ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ናትናኤል ገ/ጊዮርጊስ ከአለም ብርሀን ይግዛዉ ከቀኝ መስመር በኩል የተሻገረውን ኳስ የመከላከያዉ ተከላካይ አሚን ነስሩ ሲጨርፈዉ አግኝቷት ወደ ግብ በመቀነር የአፄዎቹን መሪነት ወደ 2ለ1 ከፍ አድርጓል።
ሁለተኛ ግብ ካስተናገዱ በኋላ የአቻነቷን ጎል ለማግኘት ተደጋጋሚ ሙከራ ማድረግ የቻሉት መከላከያዎች ዉጥናቸዉ ሰምሮ ግብ ባያስቆጥሩም በተለይ በተደጋጋሚ በአማካዩ ቢኒያም በላይ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ሲያደርጉ ተስተውሏል። በአንፃሩ የጨዋታውን ዉጤት አስጠብቀው ለመዉጣት ሲጥሩ የነበሩት አፄዎቹ ተሳክቶላቸዉ ጠንካራውን መከላከያን 2ለ1 በማሸነፍ ከመሪዉ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያላቸዉን የነጥብ ልዩነት አስጠብቀው ወጥተዋል።
በቀጣይ ፋሲል ከነማ በሳምንቱ ታላቅ ጨዋታ ከመሪዉ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ሲገናኙ በአንፃሩ መከላከያ ላለመዉረድ ከሚታትረዉ መከላከያ ጋር የሚገናኙ ይሆናል።
0 Comments
HABESHAWI SPORT